የህዳሴውን ግድብ ከደለል ለመታደግ ህብረተሰቡ 100 ቢሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከደለል ለመታደግ  ህብረተሰቡ በአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ   100 ቢሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን  ሀገር አቀፉ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት  ገለጸ።

“አንድ ዕቅድ አንድ ሪፖርት፤ ለተቀናጀ የአባይ ተፋሰስ ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ ትናንት በአሶሳ ከተማ የተጀመረው አራተኛው ሃገር አቀፍ ተፋሰስ ልማት የተሞክሮ ልውውጥ የምክክር መድረክ ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡

ሀገር አቀፉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አባል ኢንጂነር  ጌታሁን ሁሴን  በወቅቱ እንዳሉት  ጽህፈት ቤቱ በተለይ በአባይ ወንዝ ተፋሰስ የሚገኝበት ክልሎችን የተፋሰስ ልማት በቅንጅት እንዲሠሩ እያደረገ ነው፡፡

እስካሁን አርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ ጨምሮ ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል ተፋሳሰን መሰረት ባደረገ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ  100 ቢሊዮን ብር በላይ  የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ይህም የህዳሴውን ግድብ ከደለል መታደግ ብቻ ሳይሆን ለሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ግባችን ስኬት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ታደሰ በበኩላቸው በሃገሪቱ በየዓመቱ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማት  የማይከናወንበት ክልል እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ህብረተሰቡ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው ይሁንና በአፈርና ውሃ ጥበቃ የለማውን አካባቢ በባለቤትነት የሚመራው አካል አልተዋቀረም ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ልማቱ ቀጣይነቱ አስተማማኝ እንዲኖረው የአካባቢ ጥበቃና ልማት ሥራውን በባለቤትነት የሚመራ ተቋም ለማመቻቸት እንቀስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

በሃገሪቱ የተፋሰስ ልማት መጠናከር የህዳሴውን ግድብ ህልውና እንደሚያስጠብቅ የተናገሩት ደግሞ  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ  አቶ ባበክር ከሊፋ  ናቸው።

የመሬት ለምነት በማሳደግ እና የሥራ ዕድል አማራጮችን በማስፋት ስደትን ያስቀራል ብለዋል።

ከኦሮሚያ ክልል የመጡት  አርሶ አደር ሼህ አብደላ ሳኒ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው 20 ሄክታር የተራቆተ መሬት ማልማት እንደቻሉ በማውሳት ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡

በጋራ ካልሠራን የወደመውን የተፈጥሮ ሃብታችን በአጭር ጊዜ መመለስ አዳጋች ነው፤ ከፌደራል እና ክልሎች ብሎም የሚመከታቸው አካላት ተቀናጅተን እንስራ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በግላቸው የተፈጥሮ ሃብት ሥራውን ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከአማራ ክልል የመጡት  አርሶ አደር አባይነህ ብርሃኑ በበኩላቸው በምክክር መድረኩ በአካባቢያቸው ከተከናወኑ ተፋሰስ ልማት የተለየ ተሞክሮ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ከግብርና ባለሙያዎች እና ሌሎች አርሶ አደሮች በመቀናጀት ያገኙትን ተሞክሮ ተጠቅመው የተጠናከረ የአፈርና ወሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚያከናውኑም ገልጸዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ በምክክር መድረኩ ከፌደራልና ሁሉም ክልሎች የተወጣጡ ከ60 በላይ ተወካዮች እየተሳተፉ ሲሆን   በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ የአባይ ገባር ከሆነው ዳቡስ ወንዝ ዳር የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች እንደሚገበኙም ይጠበቃል።