5ኛው የብስክሌተኞችና የእግረኞች ቀን መርሐ ግብር ተካሄደ

“ከጳጕሜን እስከ ጳጉሜን እንደርሳለን!” በሚል መሪ ሀሳብ የተጀመረውን ንቅናቄ በማስቀጠል  5ኛው የብስክሌተኞችና የእግረኞች ቀን መርሐ ግብር በመላዉ የሀገሪቱ  ከተሞች መካሄዱን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር የኋላሸት ጀመረ፣ በአዲስ አበባ ከቤቴል ሚካኤል- አንፎ ስላሴ በተካሄደዉ መርሃ ግብር ተገኝተው እንዳሉት የትራፊክ አደጋን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የእግር ጉዞና የብስክሌት ትራንስፖርትን ለማበረታታት ለ5ተኛ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ ተከብሯል፡፡

ሚኒስቴሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሞተር አልባ የትራንስፖርት ስትራቴጅን በመተግበርም የትራንስፖርት አማራጮችን በማስፋት ተግባራዊ በማድረግ ላይ  እንደሚገኝ ገልፀው ብዙሃኑን የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ እና አሳታፊ የሚያደርግ ጤናማ የትራንስፖርት አማራጭችን የእግር ጉዞ፣ የብስክሌት እና በካይ ያልሆኑ ትራንስፖርቶችን መጠቀም ሊበረታታ ይገባል ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዉ የሀገሪቱ ከተሞች ለእግረኞችና ሳይክል ተጠቃሚዎች ምቹና ንጹህ መንገዶችን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡም መንገዶች የሰዎች ሰላማዊ መገናኛ መድረኮች መሆናቸውን በመገንዘብ ለመንገዶች ምቾት፣ደህንነትና ንጽህና በመረባረብ የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስርዓት በአገራችን ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲስፋፋ የበኩላችንን እንወጣ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በተጨማሪ በዕለቱም የሀገር ዉስጥ  ምርቶችን በመጠቀም ከቀርከሃ የተሠሩ ብስክሌት እና ዊልቸር  የፈጠራ ስራም ተጎብኝቷል።