ባለሃብቶች ሳይሆን ባለፀጋዎች እንሁን -ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ዛሬ የቡሬ የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክና የፌቤላ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስን መርቀው ከፍተዋል፡፡

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት አገራችን በርካታ ባለሃብቶች ቢኖራትም ሁሉም ወደ ባለፀግነት ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡

ባለሃብት ማለት ገንዘብ ያለው ማለት ሲሆን ባለፀጋ ግን ልብም ያለው ነው፣ ባለፀጋ ሰርቶ ያሰራል፤ አትርፎ ያካፍላል፤ ለወጣቶች ተስፋና ስራ ይሰጣል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒትር ዶክተር ዐብይ አህመድ፡፡

በዚህ መሰረት ፖለቲከኞች አገልጋይ፣ ባለሃብቶችም ባለፀጋ ከሆናችሁ ኢትዮጵያን ማሻገር እንችላለን ብለዋል፡፡

ግዙፉን የዘይት ፋብሪካ ላስመረቁት ባለሃብት አቶ በላይነህ ክንዴና በቡሬ የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ቀድመው በመግባት እቅዳቸውን ተግባራዊ ያደረጉት አቶ ሙላት መንገሻ ትልቅ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ፍራፍሬ ወደውጭ ልከን ጭማቂ ማስመጣት የለብንም ያሉት ዶክተር አብይ ሰሊጥና ኑግ ወደውጭ እየላክን ዘይት ስንቀበል ኖረናል፣ ስለዚህ ይህ መስተካከል አለበት ፤ ወደብልጽግና ለመሸጋገር ግብርናን በተሸለ መንገድ እሴት ጨምረን መስራት አለብን ብለዋል፡፡

ከ700 አመት በላይ እድሜ ያላት ቡሬ በንግድ እንቅስቃሴዋ ቀዳሜ እንደነበበረች ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቀደመውን ታሪኳ አስጠብቀን ማቆየት ባለመቻላችን አሁን ላይ ወደኋላ መቅረታችንን ጠቁመዋል፡፡ አሁን የተጀመሩት ትላልቅ ስራዎች ግን ቡሬን ወደቀደመ ታሪኳ ለመመለስና ለማሳደግ ትልቅ አቅም መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ዛሬ ላይ ኢትዮጵያን ለማሳነስ የሚጥሩ ሃይሎች አሉ ያሉት ጠቅላይሚኒስትር ዶክተር አብይ እነዚህ ሃይሎች ባለፉት ሶስት አመታት ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም፤ በሚቀጥሉት ሺ አመታትም አይሳካላቸውም ብለዋል፡፡ ከዚያ ይልቅ ኢትዮጵያ ወደብልጽና የምታደርገውን ጉዞ ከሌሎች አገር ወደድ ዜጎች ጋር በመሆን ትቀጥላች ብለዋል፡፡

“ኢትዮጵያን የምትወዱ በአንድ ልብ ስሩ፣ ኢትዮጵያን የምትጠሉ እና ለማፍረስ የምትጥሩ ግን የማይታሰብ፣ የማይታለም ህልም መሆኑን አውቃችሁ ከዚህ ታላቅ ህዝብ ጋር በትብብር እንድትሰሩ እጠይቃለሁ” ሲሉ ማሳሰባቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡