በወላይታ ሶዶ ከተማ ለዶ/ር ዐቢይ አህመድ እና ለለውጡ መንግስት የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ

በወላይታ ሶዶ ከተማ ለዶ/ር ዐቢይ አህመድ እና ለለውጡ መንግስት የድጋፍ ሰልፍ ዛሬ ተካሄደ፡፡

በዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሚመራው መንግስት የጀመረው የለውጥ ጉዞ ከግብ እንዲደርስ የበኩላችንን እንወጣለን የሚሉ እና ሌሎች መልዕክቶች በሰልፉ ተስተጋብተዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ከወላይታ ዞን ሁሉም አካባቢዎች ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ መንግስት ሠራተኞች፣ ነጋዴዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር እንድርያስ ጌታ በድጋፍ ሰልፉ ባስተላለፉት መልዕክት በሀገሪቱ ለመጣው ሁለንተናዊ ለውጥ የዶ/ር ዐቢይን መሪነት አድንቀዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ እና የሀገር አንድነትን ለመበታተን የቃጣውን የህወሓት ጁንታ ቡድን ከህግ በታች አድርጎ የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ያረጋገጠውን የዐቢይን መንግስት የወላይታ ሕዝብ እንደሚደግፍም ዋና አስተዳዳሪው አረጋግጠዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመሩ ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎችንም ለማስቀጠል የወላይታ ሕዝብ ከመቸውም ጊዜ በላይ እንደሚሠራ በአጽንኦት መናገራቸውን ከዞኑ ከተማ አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡