“ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ያሳዩት ቸልተኝነት አሳስቦኛል” ሲል የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት፤ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ዓርአያ መሆን ያለባቸው አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት ቸልተኛ መሆናቸውን በየመድረኩ መመልከት ተችሏል።
“የሰዎች ስብስብ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ሳያደርጉ መንቀሳቀስ፣ ርቀትን ጠብቆ አለመንቀሳቀስ በስፋት እየተስተዋሉ ነው” ብለዋል።
እንደ ዶክተር ሊያ ገለጻ፤ ለኅብረተሰቡ ዓርአያ ይሆናሉ የተባሉ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ሳያደርጉ መንቀሳቀስና ህጎች ሲጣሱም ቆሞ የመመልከት ቸልታ ታይቶባቸዋል።
የኅብረተሰቡ ቸልተኝነትና የአመራሩ ቁርጠኝነት ማነስ ሚኒስቴሩን እንዳሳሰበውም አስታውቀዋል።
“አስገዳጅ ህጎችን የማስተግበርና ከተቋማት ጋር ያለው ቅንጅት ማነስ ችግሮች እንዲባባሱ አድርጓል” ብለዋል።
የጸጥታም ይሆን የባለድርሻ አካላትና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ችግሩን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ሚኒስትሯ በአጽንኦት ጠይቀዋል።
ኮቪድ-19ን ለመከላከል ግንዛቤ ተፈጥሮ መሻሻሎች ታይተው የነበረ ቢሆንም ከመላመድና ከቸልተኝነት የተነሳ የወረርሽኙን ስርጭት በሚፈለገው ደረጃ ማስቆም እንዳልተቻለም አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት በሚካሄድ ምርመራ ኮቪድ-19 የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
በቅርቡ የሚጀመረው የኮቪድ-19 ክትባት የመከላከል ስራውን የሚተካ ባለመሆኑ ኅብረተሰቡ ከመዘናጋት እንዲቆጠብ ሳስበዋል።
“እንደ አገር የሕዝብ መሰባሰብ ግዴታ በሚሆንባቸው ቦታዎች ኮቪድ-19ን ለመከላከል የወጡ መስፈርቶች ተሟልተው ሊሆን ይገባል” ያሉት ዶክተር ሊያ፤ ተቆጣጣሪ አካላት ይህን በማስተግበር ሃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በዓለምአቀፍ ደረጃ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ተከስቶ ስጋቱ በጨመረበት በአሁኑ ወቅት መዘናጋቱ ዋጋ እንደሚያስከፍል ዶክተር ሊያ መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነወ።