ለትግራይ ክልል 9 ሚሊየን ብር የሚገመት የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

የካቲት 03/2013 (ዋልታ) – የአፋር ክልል ህዝብና መንግስት ዘጠኝ ሚሊየን ብር የሚገመት የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ ለትግራይ ክልል አስረከበ።

ድጋፉን የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኤለማ አቡበከርን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በመቀሌ ተገኝተው ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አስረክበዋል።

የምግብ ቁሳቁሱ ሩዝ፣ የፉርኖ ዱቄት፣ ስኳርና ቴምር ሲሆን አጠቃላይ ብዛቱ 2ሺህ 700 ኩንታል መሆኑ ተገልጿል።

የአፋር ክልል ላደረገው ድጋፍ በትግራይ ህዝብ ስም ምስጋና ያቀረቡት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ፤ “የአፋር ህዝብ የትግራይ ህዝብ ወንድም መሆኑን አሳይቷል” ብለዋል።

የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኤለማ አቡበከር በበኩላቸው፣  ክልላቸው ለትግራይ ያለውን አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በማረጋገጥ ድጋፉ ቀጣይነት እንደሚኖረው አመልክተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።