የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚንስቴር የ6ወር የዕቅድ አፈፃፀሙን እየገመገመ ነው

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

የካቲት 10 ቀን 2013 (ዋልታ) – የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚንስቴር የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ አመት የዕቅድ አፈፃፀሙን የሚገመግም ጉባኤ በሀረር ከተማ እያካሄደ ነው።

ሚኒስቴሩ ከተሞች የብልፅግና ማዕከል እንዲሆኑ እና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪ እንዲሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

በከተማ ልማት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታትና ዜጐችን ተጠቃሚ ማድረግ በሚችሉባቸው ዘርፎች ትኩረት ለማድረግ የውይይት መድረኩ አጋዥ ይሆናል ተብሏል::

ጉባኤውን የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከዘጠኙ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር ነው እያከናወነ የሚገኘው።

ሚኒስትሩ የከተሞች ብልፅግናን እውን ለማድረግ ያስቀመጠውን እቅድ ለማሳካት የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ አዘጋጅቶ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በዘረጋው የክትትል መንገድም የሴክተሩን ወቅታዊ አፈፃፀም ይገመግማል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚከናወነው ጉባዔ ክልሎች ከሴክተሩ አጀንዳዎች አንፃር ወቅታዊ አፈፃፀማቸውን በመገምገም መልካም ተሞክሮዎችን ለማስፋት እና መስተካከል ያለባቸውንም በጋራ ለማረም የሚያስችል ነው ሲሉ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ተናግረዋል::

የሀገሪቱ ከተሞች ቁልፍ ተልዕኮ ከተሞችን በማልማት እና ዘመናዊነትን የተላበሱ እንዲሆኑ በማድረግ የነዋሪዎችን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እና የስራ ዕድል ፈጠራዎችን ማስፋፋት በልዩ ትኩረት እየተሰራበት ይገኛል ያሉት ደግሞ የሀረሪ ክልል ፕሬዚዳንት ኦርዲን በድሪ ናቸው፡፡

(በብዙአየሁ ወንድሙ)