በአምስት ዓመታት 5 ሺህ የሶስተኛ ዲግሪ ምሩቃንን ለማፍራት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

የካቲት 10/ 2013 (ዋልታ) – የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሀገር ውስጥ ትብብርና ትስሰርን በማጠናከር በመጪዎቹ 5 ዓመታት 5ሺህ መምህራንን በሶስተኛ ዲግሪ ለማሰልጠን የሚያስችል ፕሮጀክት ትናንት ይፋ አድርጓል፡፡

በፕሮግራሙ ማብሰሪያ ስነ ስርአት ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የከፍተኛ ትምህርት መምህራንን ሁለንተናዊ ልማት ለማሳደግ ፕሮጀክቱን ወደስራ ማስገባት አስፈልጓል ብለዋል፡፡

ዶ/ር ሳሙኤል አክለውም በትብብርና ትስስር ተግባራዊ የሚሆነው “Home Grown Collaborative PhD Programs” በሁሉም መስክ ብቁ የሆኑ መምህራንን በማቅረብ የትምህርት ጥራትና አግባብነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር የምናስበውን የልማትና ብልጽግና ጉዞ ለማሳከት ብቃት ያላቸው መምህራን፣ ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎችን ማፍራት ወሳኝ ነዉ ሲሉም አክለዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው ሀገሪቱ ያላትን ሃብትና አቅም በማስተባበርና በሚገባ በመጠቀም እውቀትና ክህሎት ያለው ዜጋ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የሀገር ውሰጥና አለም አቀፍ ትብብርና ትስስሮችን በማጠናከር ለፕሮግራሙ መሳካት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው ወደሚፈለገው ደረጃ ለመድረስና የሚታሰበውን ግብ ለማሳካት የተቋማቱን አቅም መገንባትና ማጎልበት የሚኖረው ሚና ወሳኝ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የሶስተኛ ዲግሪ ስርአተ ትምህርት ክለሳና ቀረጻ፣የሀገርውሰጥና የውጭ ሀገራት ፐሮፌሰሮችን ማሰማራትና የምርምር፣የላብራቶሪ ወርክሾፕ ግብአቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል ፕሮግራሙ ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡

(ምንጭ፡- የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር)