የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተሰጥቶ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል

የካቲት 19/ 2013 (ዋልታ) የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተሰጥቶ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ሀገር አቀፍ ፈተናው በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ተጠይቋል።ትምህርት ሚኒስቴር የ2012ዓ.ም ሀገር አቀፍ ፈተና ስርጭትን አስመልክቶ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ፈተናው በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲከናወን ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ሚኒስትሩ ሀገር አቀፍ ፈተናውን በተያዘለት የግዜ ገደብ ለመስጠት እና ለማጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዲላሞ ኦተሬ በበኩላቸው ፈተናው በተያዘለት ጊዜ እንዲካሄድ በከፍተኛ ጥንቃቄና ቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከየካቲት 21 እስከ 26 ቀን 2013 ድረስ የመፈተኛ ቁሳቁሶችን የማሰራጨት ሥራ እንደሚጠናቀቅም ተገልጿል።

በመሆኑም ፈተናው በሚፈለገው አግባብ እንዲጠናቀቅ የሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት፣ የትምህርት ማህበረሰቡና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የ2012ዓ.ም ሀገር አቀፍ ፈተና ከየካቲት 29 ቀን 2013ዓ.ም ጀምሮ እንደሚሰጥ መገለፁ የሚታስ ነው።