ብሔራዊ የምክክር መድረክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሄደ

የካቲት 20/2013 (ዋልታ) – ባለፉት 6 ወራት በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ሲካሄድ የቆየው ብሔራዊ የምክክር መድረክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ማጠቃለያ በወንድማማችነት ፓርክ ተካሄደ፡፡

በ6 ወራት ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከሚገኙ የማህበረሰብ ተወካዮችና ልሂቃን ጋር “ስልጡን ምክክር ለአዲስ የተስፋ ምዕራፍ” በሚል መርህ ውይይቱ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

ምሁራን፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና የሲቪክ ማህበራት በውይይቱ ተሳታፊ ነበሩ፡፡

በምክክር መድረኮቹ ሰላምን በቤተሰብ፣ በአካባቢ ብሎም በአገር ደረጃ ማስፈን ስለሚቻልበት መንገድ ውይይት ተደርጓል፡፡

የዚህ የምክክር መድረክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ማጠቃለያ ከ2ሺህ በላይ የማህበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ውይይቱ ከየካቲት 20 እስከ 23 ተወካዮቹ በተወያዩባቸው ጉዳዮች እና በተነሱ ሀሰሳቦች ዙሪያ የሚመክር ይሆናል፡፡

በመጀመሪያ ምዕራፍ ማጠቃለያ ስነስርዓቱ ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ተገኝተዋል፡፡
(በሳሙኤል ሀጎስ)