ኢትዮጵያ ለዓለም ነፃነት ፈላጊ ህዝቦች ካበረከተቻቸው ስጦታዎች አንዱ አድዋ ነው – ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

የካቲት 23/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ ለዓለም ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ህዝቦች በሙሉ ካበረከተቻቸው ስጦታዎች አንዱ አድዋ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡

“በስልጡን ምክክር አዲስ ተስፋ ምዕራፍ” በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከማህበረሰብ ተወካዮች፣ ልሂቃንና የመንግስት አገልግሎት ተኮር ተወካዮች ጋር ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የነበረው ብሔራዊ የምክክር መድረክ ተጠናቋል፡፡

መድረኩ የአድዋ ድል በዓልን ታሳቢ በማድረግ የመድረኩን መሰረታዊ እሳቤ ከበዓሉ ጋር ለማስተሳሰር ታስቦ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡

የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል መድረኩ መጠናቀቁን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የአድዋ ድል በዓል በየጊዜው ተመንዝረው የማያልቁ ጥልቅ ረቂቅ ያለው ድል መሆኑን ጠቁመው፣ ከበዓልነት ባሻገርም ለኢትዮጵያዊያንና ለአፍሪካዊያን እንዲሁም ለመላ ጥቁር ህዝቦች መለያ የሆነ ደማቅ ታሪክ ነው ብለዋል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር  ከተሰጡት የስራ ሀላፊነት አንዱ ብሄራዊ መግባባትን እንዲፈጠር መስራት እንደመሆኑ መጠን እነዚህ የምክክር መድረኮች ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ተገልጿል፡፡

የሶስት ቀን ቆይታ በነበረው የምክክር መድረክ በተሳታፊዎች ዘንድ የጋራ አመለካከት የተገነባበት መድረክ እንደነበረ ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡