በትግራይ ክልል 5 ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ስራ መጀመራቸው ተገለጸ

የካቲት 30/2013 (ዋልታ) – በሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ሰብሳቢነት የሚመራው የብሄራዊ ድንገተኛ አደጋ አስተባባሪ ማዕከል የሚኒስትሮች ኮሚቴ ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡

በስበሰባው የኮሚቴው አባል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በትግራይ ክልል እና በመተከል ዞን በማድረግ ላይ ስላሉት የአስቸኳይ እርዳታ አቅርቦትና ስርጭት ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችን በተቀናጀና በተጠናከረ መልኩ እያቀረቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከጊዜያዊ የእርዳታ አቅርቦት ባሻገር ህዝቡን በቋሚነት መልሶ የማቋቋምና ወደ መደበኛ ህይወት የመመለስ ስራ በተጓዳኝ እየተካሄደ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

በስብሰባው ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተወካዮችም በእነርሱ በኩል ያሉ ሪፖርቶችን ያቀረቡ ሲሆን፣ የዕርዳታ ስርጭቱና ክፍፍሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ መምጣቱን አረጋግጠዋል፤ በክልሉ ያለው አጠቃላይ ሁኔታም እየተሻሻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት አምስት ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ስራ መጀመራቸውን እና ከአምስቱ ፋብሪካዎች ውስጥ አንዱ ለውጭ ገበያ አቅርቦት መጀመሩን መናገራቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡