ለትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው

መጋቢት 06/2013 (ዋልታ) – በፍጥነት ማሽከርከር ላይ በሚደረግ ቁጥጥር ለፌደራል የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የተዘጋጀ የአቅም ግንባታ ስልጠና  እየተሰጠ ነው፡፡

ስልጠናው ለ3 ቀናት የሚቆይ ሲሆን ለ105 ባለሙያዎች ይሰጣልም ተብሏል፡፡

ስልጠናው በብሉምበርግ ኢኒሼቲቭ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚደርሱ የሞት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመትን ለመቀነስ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት በትራንስፖርት ሚኒስቴር የብሔራዊ መንገድ ደህንነት ፕሮጀክት አስተባባሪ ኢ/ር ሰመረ ጅላሎ፣ ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር የሚከሰትን ጉዳት ለመቀነስ የስልጠናው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

በአለም ላይ በአማካኝ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች በየአመቱ በትራፊክ አደጋ ሳቢያ የሚሞቱ ሲሆን በኢትዮጵያ  ደግሞ በቀን 11 ሰዎች ህይወታችውን ያጣሉ፡፡

በመሆኑም መሰል ስልጠናዎች ህጉን ለማክበርም ሆነ አደጋውን ለመቀነስ ባለሙያዎች ስልጠናውን መውሰዳቸው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ተብሏል፡፡

ባለፈው በ2012 በጀት አመት 4ሺህ 133 ዜጎች በትራፊክ አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን ሲያጡ 12ሺህ ሰዎች ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ሲደርስባቸው 9ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ንብረት ወድሟል፡፡

(በህይወት አክሊሉ)