ቻይና ለኢትዮጵያ ያበረከተችው የኮቪድ-19 ክትባት ነገ እንደሚገባ ተገለፀ

መጋቢት 06/2013 (ዋልታ) – በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሸመ ቶጋ ከኦቢኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ በቻይና የተመረተዉ እና ቻይና ለኢትዮጵያ በስጦታ ያበረከተችው 300 ሺህ የኮቪድ-19 ክትባት ነገ ወደ ኢትዮጵያ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡
አምባሳደሩ የቻይና መንግስት ላደረገዉ ድጋፍ በኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበው፣ ሁለቱ ሀገራት ቫይረሱ ከተከሰተ ወዲህ በጉዳዩ ላይ በጥምረት እየሰሩ ነዉ ብለዋል፡፡

የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተሰራዉ ስራ የኢትዮጵያ የዉስጥ ጉዳይ እንደሆነ ቻይና ትገነዘባለች ያሉት አምባሳደር ተሾመ፣ ኢትዮጵያ እና ህዝቧ የዉስጥ ችግራቸዉን ለመፍታት አቅም እና ብቃትም እንደላቸው ቻይና ትረዳለች ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግኑኝነት ለማጠናከር እየተሰራ ነዉ ያሉት አምባሳደሩ፣ ቫይረሱ በኢኮኖሚዉ ላይ ያደረሰዉን ተፅዕኖ ለመቀነስ በንግድ እና ቱሪዝም ዘርፎች አብሮ ለመስራት የጋራ አቅጣጫ ተይዟል ብለዋል፡፡

(በሶሬቻ ቀበኔቻ)