በሰባት ቀናት 9,329 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል – ኢንስቲትዩቱ

መጋቢት 07/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ በሰባት ቀናት 9 ሺህ 329 ሰዎች በኮሮናቫይረስ እንደተያዙ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደጨመረ መጥቷል ያለው ኢንስቲትዩቱ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ49 ሺህ 326 ምርመራዎች 9 ሺህ 329 ግለሰቦች በኮቪድ-19 መያዛቸውን አመልክቷል፡፡
ምርመራ ከሚደረግላቸው ሰዎች ውስጥ በአማካኝ 19 በመቶ የሚሆኑት እንደተገኘባቸው የተጠቀሰ ሲሆን ካለፉት ሳምንታት ጋር ሲነጻጸር በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 32 በመቶ እንደጨመረ ኢንስቲትዩት ገልጿል፡፡
121 ግለሰቦች ህይወታቸውን ሲያጡ ካለፉት ሳምንታት ጋር ሲነጻጸር ህይወታቸውን ያጡ በ89 በመቶ መጨመሩን ገልጿል።
በወረርሽኙ ተይዘው ወደ ፅኑ ህሙማን ህክምና ክፍል የሚገቡ ግለሰቦች ቁጥር ከእለት ወደ እለት እያሻቀበ እንደሚገኝ ገልጾ፤ በትናንትናው እለት ብቻ 467 ሰው በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኙ አመልክቷል።
ወደ ኮቪድ-19 የህክምና ማዕከል ከሚገቡት 100 ግለሰቦች 69 የሚሆኑት በተለያየ መጠን ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው እንደሆኑ ጠቅሶ፤ የኮቪድ-19 ምርመራ ካደረጉት እና ቫይረሱ ከተገኝባቸው ሰዎች ውስጥ የተመረመሩበት ምክንያት ናሙና በመስጠት፣ ወደ ጤና ተቋማት በተለያዩ ምክንያት በመሄድ፣ በማህበረሰብ ቀኝት እና ዳሰሳ፣ ከኮቪድ-19 ታማሚ ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው፣ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ የኮቪድ-19 ናሙና ምርመራ ማድረግ መሆኑን ገልጿል።
“ይህ የሚያሳየው የኮቪድ-19 በማህበረሰብ ደረጃ በከፍተኛ የመዛመት ደረጃ ላይ እንዳለ ነው” ብሏል።