ሶማሌ ክልል አሁን ለደረሰበት ሰላም፣ ልማትና እድገት መከላከያ ሰራዊታችን ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል- አቶ ሙስጠፌ ሙሃመድ

መጋቢት 07/2013 (ዋልታ) – ሶማሌ ክልል አሁን ለደረሰበት ሰላም፣ ልማትና እድገት መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ሲሉ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሃመድ ገለጹ።

የሶማሌ ክልል ባለፉት በርካታ አመታት በከፍተኛ የፀጥታ ችግር ውስጥ በነበረበት ወቅት የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል የምስራቅ ዕዝ የሰራዊት አመራርና አባላት ከፍተኛ የሆነ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ብለዋል።

ከለውጡ በኋላም በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግርን በፍጥነት በመቆጣጠር ህዝባዊነቱን አስመስክሯል።

በዚህም ክልሉ ላይ ይደርስ የነበረውን ኪሳራ መቀነስ ችሏል ሲሉ ተናግረዋል።

የህወሓት ጁንታ ሃገር ለመበተን አስቦ በሰራዊቱ ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ቢሰነዝርበትም የህዝብ ልጅ የሆነው ሰራዊት ከደረሰበት ድንገተኛ ጥቃት በፍጥነት አገግሞ በወሰደው የመልሶ ማጥቃት በሁለት ሳምንት ውስጥ ጁንታውን በመደምሰስ ኢትዮጵያን ከተጋረጠባት የመፍረስ አደጋ አድኗታል።

የህወሓት ርዝራዦችና ዲጅታል ወያኔዎች ቀደም ሲል የዘረጉትን የሴራ ኔትወርክ በመጠቀም ሰራዊቱ ላይ ያልተገባና ከእውነት የራቀ ውሸት እያስተጋቡ መሆናቸውንየገለጹት አቶ ሙስጠፌ፣ ”ሰራዊታችን ግን በህዝባዊነቱ በድስፕሊኑ ተመራጭ በመሆን የጎረቤት ሃገራትን ጭምር በአስተማማኝ ሁኔታ እያስጠበቀ የሚገኝ ተወዳጅ ሰራዊት ነው” ማለታቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡