አዲሱን የአጠቃላይ ስርዓተ-ትምህርት ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችል ሰነድ ተዘጋጀ

መጋቢት 09/2013 (ዋልታ) – አዲሱን የአጠቃላይ ስርዓተ-ትምህርት ለማሻሻልና የመጨረሻ ቅርጽ አስይዞ ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችል ሰነድ መዘጋጀቱን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።
ሰነዱን በባለድርሻ አካላት ለማስገምገም የተዘጋጀ አውደ ጥናት ትናንት በቢሾፍቱ ከተማ ተካሄዷል።
በመድረኩ አጠቃላይ ሂደቱን ለባለድርሻ አካላት ያቀረቡት በሚኒስቴሩ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ምርምር ጄኔራል ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ ሸዋርገጥ ናቸው።
ዶክተር ቴዎድሮስ በገለጻቸው ከነባራዊው የአገሪቱ ትምህርት ዳሰሳዊ ጥናት በመነሳት ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በተሰናዳው ፍኖተ ካርታ ላይ በተደረገው ሰፊ ውይይት የትምህርት ፖሊሲ፣ የትምህርት ህግና የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ተመቻችቷል።
የአሁኑ መድረክም የተዘጋጀውን ስርዓተ ትምህርት የይዘት ፍሰትና ተፈላጊ የመማር ብቃት መለኪያ መርሐ ትምህርቱን በአገር ውስጥና ውጭ የብቃት አረጋጋጭ አካላት በማስገምገም በተገኘው ግብዓት በባለድርሻ አካላት የማፀደቅ ስራ መሆኑን ተናግረዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ በበኩላቸው፣ የዓለም አገሮች በስልጣኔ የቀደሙት ስርዓተ ትምህርታቸውን በየጊዜው በማሻሻል መሆኑን ጠቅሰዋል።
“ኢትዮጵያም ከነባራዊው ዓለም ሂደት ላለመለየት ስርዓተ ትምህርቷን ለውጣለች” ብለዋል።
የአገሪቱ ስርዓተ ትምህርት ብዙ ችግሮች እንዳሉበት በጥናት መረጋገጠጡን ያወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ለችግሩ መፍትሄ ለማመንጨት ኢትዮጵያውያን ምሁራን አቅም መጠቀም እንደተቻለ ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት ከቅድመ መደበኛ ትምህርት እስከ 12ኛ ክፍል ስርዓተ ትምህርት በምልዓት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
መድረኩ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነትና ሌሎች አራት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የልህቀት ማዕከላት ተሳታፊነት ቀድሞ በተሰበሰቡ ግብዓቶች መሰረት ስርዓተ-ትምህርት ለማሻሻልና የመጨረሻ ቅርጽ አስይዞ ሰነዱ ወደ ተግባር እንዲገባ ለማፅደቅ የተዘጋጀ መሆኑን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።
በሰነድ ዝግጅቱ ከተሳተፉት ምሁራን መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ዜጋና ስነምግባር ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ተስፋዬ ጅማ እንዳሉት፤ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በቀድሞው የተጓደለውን በማስተካከል የአገሪቱን ባህልና ልሳነ ብዝሃነት መሰረት አድርጎ ተዘጋጅቷል።
የመማሪያ መጽሐፎቹ ሲዘጋጁ ትውልድን ለመገንባት ትኩረትና ጥንቃቄ እንዲደረግባቸውም አስገንዝበዋል።