አስትራዜኔካ የኮቪድ-19 ክትባት ጠቀሜታው እንደሚያመዝን የአፍሪካ ህብረት ገለፀ

መጋቢት 09/2013 (ዋልታ) – የአስትራዜኔካ የኮቪድ-19 ክትባት ጥቅሞች ከሚያስከትለው የጎንዮሽ ጉዳት ይልቅ ጠቀሜታው የሚበልጥ በመሆኑ በመላው አህጉሪቱ ክትባቱ መስጠቱ እንዲቀጥል የአፍሪካ ህብረት መክሯል፡፡

የአለም ጤና ድርጅት ከአንድ ቀን በፊት ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ከ10 በላይ የአውሮፓ አገሮች ክትባቱ የደም መርጋት ችግር አስከትሏል በሚል ክትባቱን ማቆማቸው ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡

የአፍሪካ የበሽታዎች ቁጥጥር እና መከላከል ማዕከል (ሲዲሲ አፍሪካ) ዳይሬክተር ጆን ንኬንጋሶን እንደገለፁት፣ ክትባቱ ሊያደርስ ከሚችለው የጎንዮሽ ጉዳት ይልቅ ጠቀሜታው ስለሚያመዝን ክትባቱ መስጠት የጀመሩ አገሮች አጠናክረው ይቀጥሉ ብለዋል፡፡

አስትራዜኔካ እንዳመለከተው ክትባቱን ከወሰዱ 17 ሚሊዮን የእንግሊዝና የአውሮፓ ህብረት አባል አገሮች ሰዎች ላይ በተደረገ ክትትል የደም መርጋት ችግር ስለመፈጠሩ የሚያረጋግጥ መረጃ አልተገኘም፡፡

የአህጉሪቱ የበሽታ መቆጣጠሪያ ክፍል ኃላፊ በበኩላቸው እየተነሱ ያሉ አሉታዊ ምላሾች ክትትል እንደሚደረግባቸውና ለወደፊቱ በክትባቱ ላይ ለሚደረጉ ግምገማዎች ቀጥሎ ሪፖርት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

የአንዳንድ አውሮፓ አገሮችን ውሳኔ ተከትሎ የተወሰኑ የአፍሪካ አገሮች የአስትራዜኔካ ክትባትን መስጠት ለጊዜው ያቆሙ ሲሆን ዴሞክራቲክ ኮንጎ አንዷ ነች ተብሏል፡፡

በተቃራኒው በርካታ የአፍሪካ አገሮች አስትራዜኔካ ክትባት ተረክበው ለዜጎቻቸው በመስጠት ላይ ሲሆኑ አምራች ድርጅቱ ዝቅተኛና መካከለኛ አቅም ላላቸው አገሮች በነፃ እያከፋፈለ እንደሚገኝ ሮይተርስ ዋቢ አድርጎ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአውሮፓ ህብረት ውስጥ የአስትራዜኔካ ክትባት ከወሰዱ 5 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 30 ሰዎች ላይ ያልተለመደ የደም መርጋት አጋጥሟል የተባለ ሲሆን፣ የአውሮፓ መድኃኒቶች ኤጄንሲ እየመረመረ ባለበት ሂደት ውስጥ እስካሁን ድረስ ምክንያቱ ምን እንደሆነ አልተደረሰበትም፡፡