በክልሉ የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ 1,953 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ

መጋቢት 10/2013 (ዋልታ) – በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጋር በመቀናጀት ባከናወናቸው ተግባራት 1,953 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ይህንኑ ተከትሎ 18 መዝገቦችን ማደራጀቱንና 1,062 ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

በተጨማሪም 900 ዘመናዊ የጦር መሳሪያና ከ1000 በላይ ባህላዊ የጦር መሳሪያ መያዙን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ ጠቅሰዋል፡፡

በተመሳሳይ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የጁንታውን ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ በማክሸፍ ከ270 በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ የምርመራ መዝገባቸውን በማጠናቀቅ ወደ ማረሚያ እንዲወርዱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በማይካድራ ከተማ ከተፈፀመው ጭፍጨፋ ጋር ተያይዞም 130 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ማስረጃ የተገኘባቸውን በመለየት ለሕግ የማቅረብ ስራ መሰራቱን ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በህወሓት ጁንታ ቡድን በተደራጁ የኦነግ ሸኔ አባላት የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ለመቅረፍ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የጋራ ዕቅድ በማውጣት በሰሩት ስራ በርካታ የኦነግ ሸኔ አባላትም እርምጃ እንደተወሰደባቸው መናገራቸውን ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡