ክትባቱን በወሰዱ ዜጎች ላይ የደም መርጋት ችግር እንዳልተከሰተ ባለስልጣኑ አስታወቀ

መጋቢት 11/2013 (ዋልታ) – የኮቪድ-19 ክትባት መሰጠት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ክትባቱን በወሰዱ ዜጎች ላይ ምንም የደም መርጋት ችግር እንዳልተከሰተ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
በባለሥልጣኑ የመድኃኒት ምዝገባና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ አብደላ ቃሶ ክትባቱን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ ክትባቱን በወሰዱ 1 ሺህ 400 በላይ ዜጎች ላይ ምንም ዓይነት የደም መርጋት ችግር አልተከሰተም ብለዋል፡፡

ክትባቱን በወሰዱ 35 ዜጎች ቀለል ያሉና በማንኛውም ክትባት ወቅት ሊገጥሙ የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሪፖርት መደረጉን የጠቆሙት አቶ አብደላ፣ ሪፖርት የተደረጉት የጎንዮሽ ጉዳቶች ክትባት በሚሰጥበት የሰውነት ክፍል ላይ ህመም መኖር፣ ድካም፣ ራስ ምታት፣ የጡንቻ ህመም፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ የመገጣጠሚያ ህመምና ትኩሳት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ክትባቱ ከሚሰጠው ጥቅም አንፃር የጎንዮሽ ጉዳቶቹ ይሄ ነው የሚባሉ እንዳልሆነ ያመለከቱት አቶ አብደላ፣ ክትባቱ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚያግዝ በመሆኑ የጎንዮሽ ጉዳቱ አሳሳቢ አለመሆኑን ሲል ኢፕድ ዘግቧል፡፡