13 የሲሚንቶ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

ሲሚንቶ

መጋቢት 14/2013 (ዋልታ) – በከተማዋ የሲሚንቶ ምርትን በመደበቅ፣ በማከማቸት፣ አየር በአየር እና ከንግድ አድራሻ ውጪ በመሸጥ ላይ የነበሩ 13 የሲሚንቶ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡

ቢሮው የሲሚንቶ ሥርጭትና ግብይት ሂደት ላይ ባደረገው ክትትል እና ቁጥጥር 13  ጅምላና ቸርቻሪ ነጋዴዎች ምርት በመደበቅ፣ በማከማቸት፣ አየር በአየር በመሸጥ፣ ከንግድ አድራሻ ውጪ በመሸጥ፣ እንዲያከፋፍሉ ወይም እንዲሸጡ ከተፈቀደላቸው ውጪ ለሌላ አካል በመሸጥ የተለያዩ አሻጥሮችን ሲሰሩ በመገኘታቸው ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ  ወስዷል፡፡

በተለይም የሲሚንቶ ያለደረሠኝ መሸጥ የሽያጭ እና የደረሠኝ ዋጋ የመለያየት ምርትን እጅግ በተጋነነ ዋጋ በመሸጥ፣ ባልተፈቀደላቸው ወይም ባልታደሰ የንግድ ፈቃድ በመነገድ ተነጋግሮ ዋጋ በመወሰን በአጠቃላይ የሲሚንቶ ምርት በገበያ ህግ ወጪ ሆኖ ዋጋው እንዲንር እና ምርቱ እንዲሠወር በማድረግ ገበያው እንዳይረጋጋ ህገ-ወጥ ተግባር ሲፈጽሙ እንደተደረሳባቸው  ነው ቢሮው የገለፀው፡፡

በቀጣይ ከፋብሪካ የሲሚንቶ ምርት የሚረከቡ ጅምላና ቸርቻሪ ነጋዴዎች በተፈቀደው አሠራር ብቻ በትክክለኛው ዋጋ በሽያጭ እንዲያስተላልፉ እና የሥርጭትና ሽያጭን በተመለከተ   ከፋብሪካ ከማንሳታቸው በፊት ለቢሮው ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው ቢሮው አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም በሲሚንቶ ችርቻሮ ንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ነጋዴዎች በክፍለ ከተማ ከተመደቡ ጅምላ ነጋዴዎች ምርቱን በመረካከብ በተመጣጣኝ ዋጋ በደረሰኝ ለተጠቃሚዎች እንዲሸጡ ስለተረከቡት ምርትና ሽያጭ ከጅምላ ነጋዴዎች ከመረከባቸው በፊት ለክፍለከተማቸው ንግድ ጽህፈት ቤት ሪፖርት ማድረግ ይኖርባቸዋል ተብሏል፡፡

ይህን የሲሚንቶ ስርጭት መመሪያ እና ሕግን ተላልፈው በሚገኙ ማንኛውም በሲሚንቶ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 መሠረት እርምጃ እንደሚወስድ ቢሮው አሳስቧል፡፡

ነዋሪዎችም በሲሚንቶ ምርት ላይ ህገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ አካላትን ለመከላከል 8588 ነፃ የስልክ ቁጥር ጥቆማ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ መቅረቡን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡