በ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚዲያዎች ሚና ጉልህ መሆን እንዳለበት ተገለጸ

መጋቢት 16/2013 (ዋልታ) – በ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚዲያዎች ሚና ጉልህ መሆን እንዳለበት ተገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ አዘጋጅነት “የመገናኛ ብዙኃን ሀላፊነት በምርጫ” በሚል ርዕስ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መለስካቸው አመሃ ሚዲያዎች ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ ሚዛናዊ መረጃዎችን በመሥጠት ህዝቡ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ እንዲያደርግ ሊያግዙት እንደሚገባ ገልጸዋል።
አሁን ሀገሪቱ ወሳኝ የሽግግር ምዕራፍ ላይ ያለች በመሆኗ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሚዲያዎች በጥንቃቄ ሊሠሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በ1984 ዓ.ም እንደተቋቋመ የሚነገረው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ ህግ ማስከበር እና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የኢሰመጉ ዳይሬክተር አቶ ዳን ይርጋ በበኩላቸው፣ ተቋሙ በቅድመ ምርጫ፣ በድህረ ምርጫ እና በምርጫ ወቅት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመድረኩ ሚዲያዎች በምርጫ ወቅት ሊከተሏቸው የሚገቡ የአሠራር ስርዓቶችን አስመልክቶ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ይደረጋል ተብሎም ይጠበቃል።
(በድልአብ ለማ)