በአዲስ አበባ ትናንት በደረሱ የእሣት አደጋዎች ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወደመ

መጋቢት 17/2013 (ዋልታ) – ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ በደረሱ ስድስት የእሣት አደጋዎች ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የከተማ አስተዳደሩ የእሳት አደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት ከእሳት ማትረፍ እንደተቻለም ተገልጿል።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ትናንት የካቲት 16 ቀን 2013 በመዲናዋ በስድስት ቦታዎች የእሳት አደጋ ተከስቷል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት የቀብር ስፍራ እንዲሁም በወረዳ ሁለት በተለምዶ ሁለት ቁጥር ማዞሪያ በሚባለው ቦታ የእሳት አደጋዎች መከሰታቸውን ተናግረዋል።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ደግሞ በመኖሪያ ቤትና በከብቶች በረት፤ እንዲሁም በወረዳ 6 አዲሱ ሚካኤል አካባቢም የእሳት አደጋ መከሰቱን ጠቁመዋል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ በአምስት መኖሪያ ቤቶች፤ ጣፎ መስጊድ አካባቢም እንዲሁ በመኖሪያና የወፍጮ ቤት ላይ የእሳት ቃጠሎዎች መከሰታቸውን አብራርተዋል።

በነዚህ አደጋዎች በአጠቃላይ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት ማትረፍ ተችሏል ነው ያሉት።

በአደጋው አንድ ሰው ላይ ቀላልና 68 የቁም እንስሳት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አዲሱ ሚካኤል አካባቢ የተከሰተው የእሳት አደጋ  መንስኤው ኤሌክትሪክ መሆኑን የገለጹት አቶ ጉልላት የተቀሩት አካባቢዎች የአደጋ መንስኤ በፖሊስ እየተጣራ ነው ብለዋል።

እሳቱን ለመቆጣጠር 221 ሺህ 500 ሊትር ውሃ ጥቅም ላይ ሲውል 150 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተሳትፈዋል። እንዲሁም የፌዴራል፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ፖሊሶች ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር ያከናወኑት ተግባር በሰውና በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ተካላክሏል ነው የተባለው።