ቻይና ኮቪድ-19ን ለመከላከል ባህላዊና ዘመናዊ መድሃኒቶችን አጣምራ በመጠቀም ችግርን መፍታት እንደሚቻል አሳይታለች – ዶክተር አብርሃም በላይ

ዶክተር አብርሃም በላይ
መጋቢት 21/2013 (ዋልታ) – “ቻይና ኮቪድ-19ን ለመከላከል ባህላዊና ዘመናዊ መድሃኒቶችን አጣምራ በመጠቀም ነባር ዕውቀቶች ላይ ተመስርቶ ችግርን መፍታት እንደሚቻል ለዓለም አሳይታለች” ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።
ቻይና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ባህላዊ መድኃኒትን ከዘመናዊ ጋር በማጣመር ውጤት ማምጣቷን ኢትዮጵያ እንደምታደንቅም ገልጸዋል።
በቻይና ባህላዊ መድኃኒት ላይ ያተኮረ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን መከላከል ዓለም ዓቀፍ ትብብር ጉባኤ በበይነ መረብ ተካሂዷል።
በጉባኤው ላይ የቻይና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የአገራት መሪዎችና ተወካዮች ‘በቪዲዮ ኮንፍረንስ’ ተሳትፈዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ኢትዮጵያን በመወከል በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።
ዶክተር አብርሃም በንግግራቸው “ቻይና ኮቪድ-19ን ለመከላከል ባህላዊና ዘመናዊ መድሃኒቶችን አጣምራ መጠቀሟን ኢትዮጵያ ታደንቃለች” ብለዋል።
“በዚህ አካሄዷም ቻይና የዓለም ሕዝብ ነባር ዕውቀቶች ላይ ተመስርተው ችግራቸውን የሚያዩበት ዕድል መኖሩንም አሳይታለች” ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ጥንታዊት አገር እንደመሆኗ ባህላዊ መድኃኒትን ጥቅም ላይ ስታውል መቆየቷን አስታውሰዋል።
“አሁንም ቻይና እንደ አገር የሄደችበትን መንገድ በመጠቀም የኢትዮጵያ ባህላዊ መድኒቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል” ነው ያሉት።
ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ የጀመረችውን ጥረት ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ እያከናወነች መሆንዋን አብራርተዋል።
ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ትብብር ኢኮኖሚውን በመለወጥ ሂደት ሁነኛ ውጤት ማሳየቱንም አስታውሰዋል።
የቻይና የትብብር ሞዴል ለየት የሚያደርገው በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑንና መከባበርና ጣልቃ ገብነት እንደሌለው ጠቅሰዋል።
(ምንጭ፡-ኢዜአ)