የጢስ ዓባይ – ባህር ዳር የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመር ምሰሶ ስርቆት ተፈጸመበት – የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል

መጋቢት 23/2013 (ዋልታ) – ከጢስ ዓባይ የውሃ ኃይል ማመንጫ ወደ ባህር ዳር የተዘረጋው ባለ 132 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመር ምሰሶ ላይ ስርቆት እንደተፈፀመበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ገለጸ።

ከሰኞ ምሽት ጀምሮ በተፈፀሙ ስርቆቶች ስምንት ምሰሶዎች መውደቃቸውንም አመልክቷል።

በመሰረተ ልማቱ ላይ በተፈጸመው ስርቆት በአካባቢው ኃይል እንዳልተቋረጠ ማረጋገጥ እንደቻለ ያመለከተው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል፤ “ምሰሶዎቹ በመውደቃቸው ከኃይል ማመንጫው በባህር ዳር ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት ይላክ የነበረ እስከ 30 ሜጋ ዋት ኃይል መላክ አልተቻለም” ብሏል፡፡

ችግሩንም በየደረጃው የሚገኙ የመስተዳድር አካላት እንዲያውቁት የተደረገ ሲሆን የወደቁትን ምሰሶዎች በመጠገን ወደነበሩበት ለመመለስ የጥገና ስራ መጀመሩን ከየኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።