ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ለሆኑ የአፍሪካ አምባሳደሮች የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ስብሰባን በተመለከተ ገለጻ ተደረገላቸው

ሚያዝያ 05/2013 (ዋልታ) – ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ለሆኑ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ስብሰባን በተመለከተ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡

በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ኪኒሻሳ በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ስር የተካሄደውን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ስብሰባን በተመለከተ በስብሰባው ውይይት የተደረገባቸውን ጉዳዮች እና የኢትዮጵያን ዕይታ ለአምባሳደሮቹ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሶስቱም ሀገሮች ተቀባይነት ያለው ስምምነት ላይ ለመድረስ በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ስር የሚደረገው ድርድር መቀጠል እንዳለበት በጽኑ ታምናለች ተብሏል፡፡

የአባይን ውሃ አጠቃቀም በተመለከተ ሶስቱ ሀገራት ያላቸው አማራጭ በትብብር እና በአፍሪካዊ ወንድማማችነት ስሜት በጋራ መስራት እንደሆነ ለአምባሳደሮቹ ተመላክቷል፡፡

ድርድሩን ስኬታማ ለማድረግ እና መተማመንን ለማጎልበት በአውሮፓውያኑ በጁላይ 2020 በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የቢሮ ስብሰባ ወቅት በተደረሰው መግባባት እና በወጣው መግለጫ መሰረት በሁለት ደረጃ፣ በቅድሚያ በግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት እና ተያያዥ የውሃ አለቃቀቅ ጉዳዮች እና በመቀጠልም ሁሉን አቀፍ የውሃ አጠቃቀም ስምምነት ማድረግ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ኢትዮጵያ እንደምታምን ገልጸዋል።

በቀጣዩ ሐምሌ ወር የሚደረገውን የሁለተኛ ዓመት ሙሌት አስመልከቶ ኢትዮጵያ ለሱዳን እና ግብጽ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ በቅን ልቦና ተነሳሽነቱን በመውሰድ በውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር በኩል ለግብጽ እና ሱዳን አቻዎቻቸው ደብዳቤ የተላከ መሆኑ ተገልጿል።

ሚኒስትሩም ግብጽና ሱዳን የህዳሴውን ግድብ የአረብ አገሮች የውሃ ደህንነት ስጋት አድርገው የሚያቀርቡት ሁኔታ እንዳሳዘናቸው ገልጸው÷ የአባይ ተፋሰስ አገራት ሁሉ አፍሪካዊ ሆነው ሳሉ ጉዳዩን ለፖለቲካ ጠቀሜታ ሲባል የሚያራምዱት አቋም ተቀባይነት የሌለውና ሁሉም በአጽንኦት ሊገነዘበው እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወቅታዊ የድርድር ሁኔታ በተጨማሪ ለአምባሳደሮቹ የኢትዮጵያ-ሱዳን ወቅታዊ የድንበር ሁኔታን በተመለከተ፣ ኢትዮጵያ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ በሁለቱ ሀገራት መካከል በተደረጉ ስምምነቶች እና ባሉት የድንበር አሰራር ማዕቀፎች አማካኝነት በድርድር ለመፍታት ያላትን ቁርጠኝነት ገልጻለች።

አምባሳደሮቹም በበኩላቸው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ ስር “አፍሪካዊ መፍትሔ፣ ለአፍሪካ ችግር” በሚለው መርህ መሰረት ውጤታማ እንዲሆን ማስቻል እንደሚገባ ገልጸው ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በዚሁ ማዕቀፍ ድርድራቸውን እንዲቀጥሉ አበረታተዋል።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንዳመላከተው የኢትዮጵያ-ሱዳን ድንበርን በተመለከተ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ ችግሮቹን ለመፍታት የወሰደችውን አቋም እንደሚያደንቁ ገልጸዋል፡፡