በፋርማሲዮቲካል ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ መኖሩ ተገለጸ

ሚያዝያ 07/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ በፋርማሲዮቲካል ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ መኖሩ ተገለጸ፡፡

በአልጀሪያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በአልጀሪያ ከሚገኘው የፋርማሲዮቲካል ኩባንያ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋቶም አካሰም ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ አምባሳደር ነብያት በኢትዮጵያ በፋርማሲዮቲካል ዘርፍ ለሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ያሉትን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች በተመለከተ ለፕሬዘዳንቷ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የፋርማሲዮቲካል ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ መንግሰት ልዩ ትኩረት ከሚሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ መሆኑን በመጥቀስ፣ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ራሱን የቻለ የኢንዱስትሪ ፓርክ ተገንብቶ ለባለሀብቶች ክፍት መደረጉንና፣ ከቀረጥ ነጻና የእፎይታ ጊዜን ጨምሮ የተለያዩ ማበረታቻዎች እንደሚደረጉ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያና አልጀሪያ መካከል በፋርማሲዮቲካል ዘርፍ የሚደረገውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ ከሁለቱም አገራት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶችን ትስስር መፍጠርና የበለጠ ተቀራርበው መስራት የሚችሉበትን እድል ማመቻቸት እንደሚገባ ስምምነት ላይ መደረሱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።