ሚያዝያ 07/2013 (ዋልታ) – የአሜሪካ መንግሥት በሩሲያ ላይ መጠነ ሰፊ ማዕቀብ ሊጥል እንደሆነ ተገለጸ፡፡
አሜሪካ ማዕቀቡ የምትጥለው ሩሲያ ባደረገችው የሳይበር ጥቃት አፀፋዊ ምላሽ እንደሆነ አስታውቃለች።
ከዚህም በተጨማሪ አሜሪካ በባለፈው አመት ባደረገችው ምርጫ ሩሲያ ጣልቃ ገብታለች በማለትም ትወነጅላለች።
ማዕቀቡ በያዝነው ሳምንት ሃሙስ ይጀምራል ተብሎ የሚታመን ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዙር 30 የሩሲያ ተቋማትን ጨምሮ 10 ሩሲያውያን እንደሚባረሩ ተገልጿል። ኢላማ ከሆኑት መካከል ዲፕሎማቶችም አሉበት ተብሏል።
የጆ ባይደን አስተዳደር በተጨማሪ የአሜሪካ የፋይናንስ ተቋማት ከሰኔ ጀምሮ የሩሲያ ቦንድ ከመግዛት እንደሚታገዱም ምንጮችን ጠቅሶ ሲቢኤስ ዘግቧል።
የአሜሪካና የሩሲያ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ መጥቶ ወደ ባላንጣነት ሊሸጋገሩ ይችላል በሚባልበት ወቅት ነው ይህ ማዕቀብ የሚጣለው።
ጆ ባይደንና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ማክሰኞ እለት ባደረጉት የስልክ ልውውጥ ባይደን አገራቸው ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር “ቆፍጠን ያለ እርምጃ ትወስዳለች” ብለዋል።
ባይደን ከዚህ በተጨማሪ ከፑቲን ጋር “ሶስተኛ አገር እንገናኝ” የሚል እቅድ ያቀረቡ ሲሆን፣ ሁለቱም መሪዎች አብረው የሚሰሩባቸውን ዘርፎችም ለማየት ያስችላቸዋል ተብሏል።
በባለፈው ወር ጆ ባይደን ከአንድ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ “ፑቲን ነፍሰ ገዳይ ነው ብለው ያስባሉ ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሻቸው “አዎ” የሚል ነበር።
ውስብስብ በተባለው ሩሲያን ጥፋተኛ ባደረገው የሳይበር ጥቃት ዒላማ ከሆኑት የአሜሪካ ኢነርጂ ቢሮ እና ፌደራል መሥሪያ ቤቶች በተጨማሪ የመከላከያ፣ የአገር ውስጥ ደኅንነት (ሆምላንድ ሴኩሪቲ)፣ የአሜሪካ ግምጃ ቤትና ንግድ ሚኒስቴር ዳታዎች ዒላማ መደረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።