ዜጎች የምርጫ ካርድ ወስደው ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ሊጠቀሙ እንደሚገባ ተጠቆመ

ሚያዚያ 08/2013 (ዋልታ) – የምርጫ ካርድ ወስደው ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ሊጠቀሙ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ስድስተኛውን ብሔራዊ ምርጫ  አስመልክቶ  መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

በመግለጫውም “በጉጉት የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ምርጫ በአገራችን የሚካሄደው የመጀመሪያው ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ይሆናል ተብሎ ይታመናል” ብሏል።

ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ አገሪቱን እያስተዳደረ የሚገኘው አመራር የፖለቲካውን ምህዳር ለማስፋት እና ዴሞክራሲያዊና እውቀት ተኮር የሆነ ምቹ ከባቢ እንዲኖር ለማስቻል በቁርጠኝነት ዴሞክራሲያዊ ጎዳና መያዙን ገልጿል።

ይህ ግብ ያለ ምንም ተግዳሮት እውን የሚሆን አይደለም ያለው ፅህፈት ቤቱ፥ ይሁን እንጂ የፌደራል መንግሥት ዴሞክራሲያዊነትን ይዞ ለመጓዝ ያለውን ጽኑ ፍላጎት ሳያወላውል መቀጠሉን አውስቷል።

በመሆኑም ሊካሄድ ጥቂት ሳምንታት በቀሩት አገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ዜጎች የምርጫ ካርድ ወስደው ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ ጽህፈት ቤቱ አስገነዝቧል።

እስካሁን ድረስ፣ የፌደራል መንግሥት የመጀመሪያውን ነጻ፣ ፍትሐዊ እና ሰላማዊ ምርጫ ለማከናወን ያለው ቁርጠኝነት፣ ይህንን ግብ ለማሳካት በሚያካሂደው ያልተቋረጠ ዝግጅት አማካኝነት የተመሰከረ መሆኑንም ገልጿል።

ሰላማዊ እና ሕጋዊ ምርጫ እንዲካሄድ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ከብሔራዊ መረጃና የደህንነት አገልግሎት፣ ከመከላከያ ሚኒስቴር እና ከክልል አመራሮች ተውጣጥቶ ሀገር አቀፍ የምርጫ ደህንነት ኮሚቴ በመንግሥት መዋቀሩንም ጠቅሷል።