በአርብቶ አደሩ ዘንድ የሚከሰቱ በሽታዎችን መቆጣጠርና መከላከል ላይ ያተኮረ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው

ሚያዝያ 09/2013 (ዋልታ) – በአርብቶ አደሩ ዘንድ አዲስ ለሚፈጠሩ እና ዳግም ለሚከሰቱ በሽታዎችን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል “አንድ የጤና አተገባበር ወይም ዋን ሄልዝ አፕሮች ቱ ኮንትሮል ኢመርጂንግ ኤንድ ሪኢመርጂንግ ዲዝዝ ኢን ፖስቶራል ላይፍ” የተሰኘ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲው የጤና ኮሌጅ አዘጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ ኮንፈረንስ ላይ በዘርፉ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን ያካሄዱ ተመራማሪዎች ጥናቶቻቸውን እያቀረቡ ነው፡፡

የቦረና ዞን በቤት እንስሳት እርባታ የሚታወቅ ሲሆን፣ የአካባቢው ማህበረሰብም ኑሮውን የመሠረተው በእንስሳት እርባታ በመሆኑ በእንስሳቶቹ እና በማህበረሰቡ መካከል ያለው ግንኙነት በንክኪ የተቆራኘ ነው። በዚህም አማካኝነት ከሰው ወደ እንስሳት እና ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች መስፋፋታቸውን በመድረኩ ላይ የቀረቡ ጥናቶች ያመለክታሉ።

ይህም ችግር ደግሞ የአንድ አከባቢ ብቻ ሳይሆን ችግሩ ሀገራዊ መሆኑ ነው የተገለጸው።

በቀጥታ የችግሩ ተጠቂ የሆነውን የአርብቶ አደሩን ብሎም የሀገሪቷን ጤና ለመጠበቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በሚካሄደው ውይይቱ የአከባቢውን ማህበረሰብ ጨምሮ ምሁራን፣ ተማሪዎች እና ተመራማሪዎች በአካል እና በበይነ መረብ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እየተሣተፉ ይገኛሉ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ችግር መሠረት ያደረጉ ስራዎችን በስፋት እየሰራ መሆኑን ተናግረው፣ ይህም አድማሱን እያሰፋ ይሄዳል ብለዋል።

(በሚልኪያስ አዱኛ)