ከሻሸመኔ ወደ ሞያሌ ሲጓጓዝ የነበረ ከዘጠኝ ኩንታል በላይ አደንዛዥ ዕጽ በቁጥጥር ስር ዋለ

ሚያዝያ 11/2013 (ዋልታ) – ከሻሸመኔ ወደ ሞያሌ ሲጓጓዝ የነበረ ካናቢስ የተባለ ዘጠኝ ኩንታል ተኩል አደንዛዥ ዕጽ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
በኦሮሚያ ክልል የቦረና ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከል አስተባባሪ ተወካይ ዋና ሳጂን ሲሳይ መገርሳ እንደገለጹት፤ ዕፁ የተገኘው ሚያዝያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም በዞኑ ዋጭሌ ወረዳ ዌብ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡
አደንዛዥ ዕፁ መነሻው ሻሸመኔ ሆኖ ወደ ሞያሌ ለማጓጓዝ ታስቦ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3- 70251 አዲስ አበባ በሆነ አይሱዙ ተሽከርካሪ ላይ ተጭኖ ዌብ ቀበሌ እንደደረስ በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ተናግረዋል።
አሽከርካሪው ለጊዜው ከአካባቢው ሸሽቶ ቢያመልጥም ፖሊስ ክትትል እያደረገበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አደንዛዥ ዕጹ ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት እንዳለው ያመለከቱት ዋና ሳጂን ሲሳይ በአቋራጭ ለመበልጸግ በህገወጥ ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦችን በማጋለጥ የዞኑ ህዝብ የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ህገ ወጦችን ለመከላከል ከፍትህ አካላት የተውጣጣና በዞኑ አስተዳዳር የሚመራ የጸረ ኮንትሮባንድ ግብረ ሃይል መቋቋሙንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በቦረና ዞን ህዝብ ጥቆማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 17 ሺህ 600 ኪሎ ግራም የሚመዝን አደንዛዥ ዕጽ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉንም አስታውሰዋል፡፡