ናሳ ማርስ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሄሊኮፕተር አበረረ

ሚያዝያ 11/2013 (ዋልታ) – የአሜሪካ የህዋ ምርምር ተቋም ናሳ አነስተኛ ሄሊኮፕተርን በማርስ ፕላኔት ላይ በተሳካ ሁኔታ አበረረ፡፡
ናሳ ‘ኢንጂኒዩቲ’ በመባል የምትጠራውን ሰው አልባ ሄሊኮፕተር በፕላኔቷ ላይ ማብረር የቻለው ከአንድ ደቂቃ በታች ለሆነ ጊዜ ቢሆንም፤ በሌላ የዓለም ክፍል ላይ ከሚገኝ ስፍራ ቁጥጥር የሚደረግለትን የመጀመሪያውን በረራ ማድረግ በመቻሉ ደስታን ፈጥሯል።
ሄሊኮፕተሯ በማርስ ላይ በረራ ማድረጓን በተመለከተ በፕላኔቷ ላይ ከሚገኝ ሳተላይት ወደ መሬት ከተላለፈ መረጃ ለማረጋገጥ ተችሏል።
የህዋ ምርምር ተቋሙ ከዚህ ሙከራው በኋላ ተመሳሳይ ያልተሞከሩ በረራዎችን ወደፊት እንደሚያከናውን ገልጿል፡፡
በረራውን ያደረገችው ሄሊኮፕተር ወደ ማርስ የተወሰደችው ‘ፐርሲቨራንስ’ በተባለችው የናሳ መንኮራኩር ሲሆን፤ መንኮራኩሯ ባለፈው የካቲት ወር በቀይዋ ፕላኔት ላይ ማረፏን ቢቢሲ አስታውሷል።