ምክር ቤቱ ተቋማዊ ሪፎርም እያደረገ መሆኑን ገለጸ

ሚያዚያ 12/2013 (ዋልታ) – የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገመንግስታዊ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት ተቋማዊ ሪሮርም እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ተቋማዊ ሪፎርሙን በተመለከተ ምክር ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ይገኛል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ ምክር ቤቱ የህገ መንግስቱ ጠባቂ ተቋም መሆኑን ገልጸው በህገ መንግስት አተረጓጎም ስርዓት መርሆችና ሂደት በዝርዝር ባለመደንገጋቸው ምክንያት በተለይም በአቤቱታ አቀራረብ፣ ውሳኔ አሰጣጥና አፈጻጸም ዙሪያ ክፍተት ይስተዋላል ብለዋል፡፡

ሪፎርሙ ሀገራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም መገንባት፣ ውጤታማ ሽግግርና ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ማረጋገጥ፣ የህገ መንግስት የበላይነትና ህገ መንግስታዊነትን ማረጋገጥ እንዲሁም ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም መገንባት በሚሉት ትኩረት አድርጓል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተደረሰው ስምምነትና በተከናወነው የመጀመሪያ ዙር ጥናት ሪፖርት ላይ እየተወያየ ሲሆን በህገ መንግስት፣ የበላይነትና ህገ መንግስታዊነትን ማረጋገጥ ላይ አተኩሯል፡፡

(በሰለሞን በየነ)