የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓለም አቀፍ መሆን የሚያስችለውን ጥናት አስጀመረ

ሚያዚያ 14/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓለም አቀፍ ባንክ ለመሆን የሚያስችለውን ጥናት አስጀመረ።
በጥናቱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የዓለም ባንክ ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራሮች፣ የቦርድ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል።
ለጥናቱ በወጣው ጨረታ በባንክ ኢንዱስትሪው የተሻለ ልምድ ያላቸው አራት ዓለም አቀፍ ተቋማት ተሳትፈው “ናካንዚ” የተሰኘው ድርጅት ጥናቱን ለማካሄድ ማሸነፉ ተገልጿል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ እንዳሉት በጥናቱ ባንኩ ዓለም አቀፍ ባንክ ሆኖ የተሻለ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያደርጉ ተግባራት ላይ ትኩረት ይደረጋል።
ጥናቱ በብድር አሰጣጥ፣ በገንዘብ ማስቀመጥና ክፍያ፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በአደረጃጀትና በሰው ኃይል አስተዳደር ጉዳዮች ላይ በማተኮር እንደሚከናወንም አስታውቀዋል።
የባንኩን የፋይናንስ አቅርቦት አስተማማኝ ለማድረግ የዳሰሳ ጥናቱ የራሱን እገዛ እንደሚያደርግ ነው ፕሬዚዳንቱ የገለጹት።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ935 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሃብት ያለው ሲሆን ተቀማጭ ካፒታሉም ከ700 ቢሊዮን በላይ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።