የተፎካካሪ ፓርቲዎች የተጠቀሙት ነፃ የአየር ሰዓት ጊዜ 51.3% መሆኑ ተገለፀ

ሚያዝያ 14/2013 (ዋልታ) – የተፎካካሪ ፓርቲዎች ከተሰጣቸው ነፃ የአየር ሰዓት ጊዜ ውስጥ እስካሁን የተጠቀሙት 51 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ መሆኑ ተገለፀ።
በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ ”በርካታ” ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ የተሰጣቸውን ነፃ የአየር ሰዓት በአግባቡ እየተጠቀሙበት አለመሆኑም ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት በአዲስ አበባ አካሂዷል። በውይይቱ ከተለያየ መገናኛ ብዙሃን የምርጫ ዴስክ ተወክለው የመጡ ሃላፊዎች እንደገለጹት ፓርቲዎቹ የተሰጣቸውን ነፃ የአየር ሰዓት ጊዜ እስካሁን በአግባቡ መጠቀም አልቻሉም።
በዚህም ”በርካታ” ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ በመገናኛ ብዙሃን የተሰጣቸውን ነፃ የአየር ሰዓት በአግባቡ እየተጠቀሙበት አለመሆኑ ተገልጿል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡት ፓርቲዎች መካከል አንዳንዶቹ የተሰጣቸውን የአየር ሰአት በአግባቡ ያልተጠቀሙት ሚዲያዎቹ መልዕክቶቻችሁን ቀርፃችሁ ከ48 ሰዓት በፊት አምጡ በማለታቸውና የበጀት እጥረትም ስለገጠማቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ከ2 ሳምንት በፊት ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮችና ሃሳቦቻቸውን እንዲያቀርቡ ነፃ የጋዜጣ አምድ እና የአየር ጊዜ ድልድል ማድረጉ የሚታወስ ነው።