ሚያዝያ 15/2013 (ዋልታ) – “ችግኝ ተከላ ለሰላም” በሚል መሪ ቃል የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የችግኝ ተከላ መርኃግብር አካሔደ፡፡
በየአመቱ የሚከበረውን የመሬት ቀንን በማስመልከት ችግኝ ተከላ ለሰላም በሚል መሪ ሀሳብ ግሪን ላንድ ዲቭፕሎመንት ፋውንዴሽን ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን በሰሜን ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ አድግሴ ቀበሌ ከ1 ሺህ በላይ ችግኞችን ተክለዋል።
የአካባቢውን ተፈጥሯዊ ሁኔታ ያገናዘበና ለአየር ንብረቱ ጉልህ ሚና አላቸው የተባሉ ከ1 ሺህ በላይ ችግኞች በጥናትና ምርምር ታግዘው የተተከሉ ሲሆን፣ ዓላማውም በአካባቢው በየጊዜው የሚከሰተውን የእሳት አደጋ ለመግታት ችግኞችን መትከል፤ ከተከሉ በኋላም መንከባከብ የሚል እሳቤ እንዳለው ተገልጿል።
የመሬት ቀን በማስመልከት ለመሬቶች ክብካቤ የሚሻው መሆኑን ለማሳየት ያለመ እንደሆነም የተነገረለት የችግኝ ተከላው ችግኝ የሚተከለው የክረምት ወቅትን ተጠብቆ ብቻ አለመሆኑን ግንዛቤ ለመፍጠርም ነው ተብሏል።
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ጀጃው ደማሙ እንደገለፁት፣ የሚፈለገው ውጤት የሚመጣው ችግኞችን በመትከል ብቻ ሳይሆን በመንከባከብ ጭምር በመሆኑ በችግኝ መትከሉና በመንከባከቡ በኩል የአርሶ አደሩ ተሳታፊነት ወሳኝነት አለው፡፡
በዚህም የአርሶ አደሩን ተሳታፊነት ለማጉላት ዩኒቨርሲቲው እንቅስቃሴውን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ግሪን ላንድ ፋውንዴሽን ከ14 ዓመታት በላይ በአረንጓዴ ልማት ላይ ሲሰራ የቆየ ሲሆን፣ በቀጣይ ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
(በዙፋን አምባቸው)