ብሔራዊ ባንክ የብር ቅየራ ክንውንን አስመልክቶ የዕውቅና መርሃግብር እያካሄደ ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በስኬት ያጠናቀቀውን የብር ቅየራ ሥራ ክንውን አስመልክቶ የዕውቅና እና የምስጋና መርሃግብር እያካሄደ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ በብር ኖት ቅየራው ምክንያት 7 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች አዳዲስ አካውንት መክፈታቸውን ገልጸው፣ በዚህም 126 ቢሊየን ብር በመሰብሰቡ ባንኮች የነበረባቸው የገንዘብ ችግር ተቀርፏል ብለዋል።

የብር ቅየራ ሂደቱ በተሳካ ሁኔታ የተጠናቀቀ ቢሆንም እንደ ሀሰተኛ የብር ኖቶች ዝውውርና መሰል ችግሮች ተከስተው የነበሩ ሲሆን ከተባባሪ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ችግሩ መቀረፉን አንስተዋል።

በተጨማሪም በትግራይ ክልል በተፈጠረው ችግር ምክንያት በክልሉ የቅየራ ሂደቱ የተጓተተ እንደነበር አንስተዋል።

ዶ/ር ይናገር የብር ቅየራው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ድጋፍና እገዛ ያደረጉ አአካላትን አመስግነዋል።

(በብርሃኑ አበራ)