በተሽከርካሪ አካል ውስጥ ሽጉጦች በድብቅ ሲያጓጓዝ የተገኘ አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

ሚያዚያ 19/2013 (ዋልታ) – በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ወረዳ በተሽከርካሪ አካል ውስጥ 100 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ በድብቅ ሲያጓጉዝ ተገኝቷል ያለውን አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ዋና ክፍል ሀላፊ ኮማንደር ውብነህ አስናቀው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ሽጉጡ የተገኘው ዛሬ ከቀኑ ስምንት ሰአት ተኩል አካባቢ በሳንጃ ከተማ የፍተሻ ኬላ ላይ ነው።

የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3 -17647አማ ” አባዱላ ” የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ወንበር ስር በረቀቀ መንገድ በተዘጋጀ ስፍራ በድብቅ ሲጓጓዝ ማግኘት እንደተቻለም ተገልጿል።

ፖሊስና የጉምሩክ ፈታሾች በጋራ ባደረጉት ፍተሻ በቁጥጥር ስር የዋለው ህገ ወጥ ሽጉጡ መነሻቸው ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ አብደራፊ ከተማ ሆኖ ወደ ጎንደር ከተማ ለማስገባት ታስቦ የነበረ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ህገ-ወጥ ሽጉጡ በድብቅ ሲያጓጉዝ የተገኘው አሽከርካሪ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበትመሆኑን ኮማንደር ውብነህ ገልጸዋል።

ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የሀገር ሰላም የማደፍረስ ተልዕኮ ያለው ዋነኛ ወንጀል በመሆኑ ይሄን ለመቆጣጠር ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡