«ጉሚ በለል» የውይይት መድረክ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽ/ት ቤት ተካሄደ

ግንቦት 06/2013 (ዋልታ) – ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን የሚያደርገው «ጉሚ በለል» የተሰኘ ሳምንታዊ የውይይት መድረክ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ተካሄደ፡፡
በዚህ ሳምንትም ፌደራሊዝም እና ሀገር ግንባታ በሚል ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እና ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
የፌደራል ሥርዓቱን መልካም ጎኖች አጠናክሮ ማስቀጠል እና ክፍተቶችን ማረም የሚያስችሉ የተለያዩ ሃሳቦች በውይይቱ ተነስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ላለፉት ረጅም አመታት በፌደራሊዝም ስረዓት ስትመራ የቆየች ሀገር እንደመሆኗ ብዝሃነትን መሰረት ያደረገ ስረዓት እንዳላት ብዙዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡
ብዘሃነትን ለምታስተናግደው ሀገር አትዮጵያ ፌደራሊዝም ወሳኝ መሆኑን የሚያነሱት ምሁራኑ ሁሉን አካታች ለማድረግ ግን ሊሻሻሉ የሚገባቸው ስረዓቶችን አሉ ብለዋል፡፡
አኩሪ ታሪክ፣ ያልተተረኩ ቱባ ባህሎች እና ትውፊቶች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ አሁን ላይ እኩይ አላማን ባነገቡ አካላት ስትናጥ ይስተዋላል፣ በዚህም ከታሪኳ ጋር ፈጽሞ የማይሄደውን ጽንፈኝነት ወደ ኋላ በመጣል ሁሉም በሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ተብሏል፡፡
በሚቀጥሉት ሳምንታትም ሀገራዊ ሃሳቦች እና መፍትሄዎች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ውይይት እንደሚቀጥል ተመላክቷል፡፡
(በሜሮን መስፍን)