ግንቦት 11/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ ለሁለት ወራት የሚዘልቅ “ዳግም_ትኩረት ለኮቪድ-19” ከተማ አቀፍ የንቅናቄ መርሐ ግብር ይፋ ተደርጓል፡፡
የንቅናቄ መርሃግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተጀምሯል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተበባሪ እና የከተማዋ የኮቪድ 19 መከላከል ግብረ ሃይል ሰብሳቢ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ በከተማው አሁን ያለውን የኮቪድ -19 ስርጭት በተለመደ የአደጋ ምላሽ አካሄድ መመለስ አይቻልም ብለዋል፡፡
የቫይረሱን ስርጭት የበለጠ ሊያስፋፉ የሚችሉ ክንውኖች እንዳይኖሩ አመራሩ ጥብቅ ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ የኮቪድ 19 ስርጭትን መቆጣጠር እና የሞት መጠኑንም መቀነስ የሚቻለው ሁሉም ተቋማት በቅንጅት ሲሰሩ ነው ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከግንዛቤ ንቅናቄዎች በተጨማሪ የሆስፒታሎችን የመመርመር አቅምን ማሳደግ፣ የክትባት ሽፋኑን ተደራሽ ማድረግ እና የፅኑ ህክምና ማዕከላትን በማሳደግ ላይ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለተከታታይ ሁለት ወራት በሚቆየው “የዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 ንቅናቄ” በመመሪያ የተቀመጡ ክልከላዎችን እና የመከላከል ስታንዳርዶችን ሳያሟሉ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማትና የስራ ሃላፊዎች ላይ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ በመርሃግብሩ ላይ ተገልጿል መባሉን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬተሪ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡