የአማራ ልማት ማህበር የአባላቱን ብዛት ለማሳደግና ማህበራዊ ድጋፉን ለማጠናከር እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ

ግንቦት 13/2013 (ዋልታ) – ከሁለት አመታት ወዲህ በትምህርትና ጤና ዘርፍ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው የአማራ ልማት ማህበር የአባላቱን ብዛት ለማሳደግና ማህበራዊ ድጋፉን ለማጠናከር እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ።

ማህበሩ በአዲስ አበባ ለሚገነባው የአማራ ባህል ማዕከል የገቢ ማሰባሰቢያና የውይይት ፕሮግራም አዘጋጅቷል፡፡

ከ45 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት የሚነገርለት የአማራ ልማት ማህበር ካለፉት ሁለት አመት ወዲህ በትምህርትና ጤና ዘርፍ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ በክልሉ በርካታ ስራዎች እንደሰራ በመድረኩ ላይ ገልጿል፡፡

በክልሉ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ለተጎዱ ወገኖች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ 121 ሚሊየን ብር በማሰባሰብ ድጋፍ እንዳደረገም ጠቁሟል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ያስገነባቸው ትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች ማህበሩን ያስመሰገኑት ተግባራት ናቸው ተብሏል።

በማህበሩ እንቅስቃሴና አዲስ አበባ  ላይ ለመገንባት በታሰበው የአማራ ባህል ማዕከል ዙሪያ በመጪው እሁድ ለመወያየት ቀነ ቀጠሮ የተያዘ ሲሆን፣ ለባህል ማዕከሉ ግንባታ የሚሆን ገቢ ለማሰባሰብና የማህበሩን ስራዎች ለማጠናከር እንደሚሰራ ነው የተገለፀው፡፡ በዚህም ስለ ባህል ማዕከሉ ገልፃ ተደርጓል፡፡

የአማራ ልማት ማህበር በትምህርትና ጤና ዘርፍ ያስጀመራቸውን መልካም ተግባራት አጠናክሮ ለማስቀጠልና የማዕከሉን ግንባታ እውን ለማድረግ የአባላቱና ከአባላቱ ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እገዛ እንደሚያሰፈልግ ነው ጥሪ ቀርቧል፡፡

የአማራ ልማት ማህበር ለሚያደርገው ማህበራዊ ድጋፍ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እገዛ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ድጋፉ የበለጠ እንዲያድግና እንዲሰፋም ይጠበቃል ነው የተባለው፡፡

ማህበሩ እሁድ በአዲስ አበባ አንድነት ፓርክ በሚያደርገው የገቢ ማሰባሰቢያና ውይይት ፕሮግራም ላይ አባላቱና ደጋፊዎቹ እንደገኙም ጥሪ ቀርቧል፡፡

(በደምሰው በነበሩ)