ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ ከ70% በላይ የአየር ሠዓት መጠቀማቸው ተገለጸ


ግንቦት 14/2013 (ዋልታ) –
በስድስተኛ ሀገራዊ ምርጫ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ ከተመደበላቸው ነጻ የአየር ሠዓት እስካሁን ከ70 በመቶ በላይ መጠቀማቸውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ።
በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ለተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች ነጻ የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ተመድቦላቸው የምርጫ ቅስቀሳ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።
የባለስልጣኑ የንግድ ብሮድካስት ክትትል ዳይሬክተር አቶ ዴሬሳ ተረፈ ለኢዜአ እንደገለጹት ቀደም ሲል በወጣው የድምጽ መስጫ ቀን መርሃ ግብር መሰረት የፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ከመጋቢት 30 እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም እንደነበር አስታውሰዋል።
ሆኖም የምርጫው ቀን በመራዘሙ የምርጫ ቅስቀሳውም ምርጫውን ለማካሄድ 4 ቀን እስከሚቀር ድረስ እንደሚካሄድ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ነጻ የአየር ሠዓት አጠቃቀምን በተመለከተ አፈጻጸሙ ከፓርቲ ፓርቲ እንደሚለያይ የገለጹት አቶ ዴሬሳ፣ “እስካሁን ምንም የአየር ሠዓት ያልተጠቀመ ፓርቲም አለ” ብለዋል።
የምርጫ ቅስቀሳ ከተጀመረበት ጊዜ አንጻር ሲታይ አሁን የፓርቲዎች አጠቃቀም መሻሻል ማሳየቱንም ገልጸዋል።
የምርጫ ቅስቀሳው ላይ ፓርቲዎች የራሳቸውን ፖሊሲ ከማስተዋወቅ ይልቅ መሬት ላይ ያለውን ሥራ የማጥላላት ሁኔታ ላይ ሲያተኩሩ ተስተውሏል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ፓርቲዎች ለአገር በሚጠቅሙ ሀሳቦችና የፖሊሲ አማራጮች ላይ እንዲያተኩሩ መምከራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
“አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ሆነው የክልል ሚዲያ ላይ የተመደበላቸውን የአየር ሠዓት ያለመጠቀም እንዲሁም ክልላዊ ፓርቲ በብሔራዊ ሚዲያ ያለመጠቀም ሁኔታዎች ተስተውሏል” ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃን በሚፈለገው መልኩ ፓርቲዎችን እያስተናገዱ ቢሆንም ፓርቱዎች የተመደበላቸውን የአየር ሠዓት ያለመጠቀም ችግር መኖሩንም ጠቁመዋል።
ከስርጭት ተደራሽነትና ተደማጭነት ጋር በተያያዘ ክፍተት እንዳለ በፓርቲዎች መነሳቱን አስታውሰው፣ ለግጭት የሚያነሳሱ ይዘቶች በማስተላለፍ በኩል የጎላ ችግር እንደሌለ ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ ፓርቲዎች ቅስቀሳውን በመገናኛ ብዙሃን እንዲያካሂዱ ከማመቻቸት ባሻገር በአግባቡ ያልተጠቀመውን ፓርቲ ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ካካሄደ በኋላ የምርጫው ድምጽ መስጫ ቀን እንዲራዘምና የ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ የድምጽ መስጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲሆን መወሰኑ ይታወቃል።