ከአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ወጪ ንግድ 433 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር መገኘቱ ተገለጸ

አቶ ወንዳለ ሃብታሙ

ግንቦት 16/2013 (ዋልታ) – ከአበባ አትክልትና ፍራፍሬ (የሆርቲካልቸር) ምርቶች የውጭ ንግድ በ10 ወራት ውስጥ 433 ነጥብ 2 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የሆርቲካልቸር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንዳለ ሃብታሙ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ በወጪ ንግድ ከአበባ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ተገኝቷል። በዚህም በ10 ወራት ውስጥ ከዘርፉ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 433 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።

በኢትዮጵያ ከአጠቃላዩ የሆርቲካልቸር ምርት 97 በመቶ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚቀርብ ሲሆን፣ ሶስት በመቶው ብቻ ለውጭ ገበያ ይቀርባል ያሉት አቶ ወንዳለ፣ ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ምርት ውስጥ ከ80 በመቶ የሆነውን ድርሻ የሚይዘው የአበባ ምርት መሆኑን ገልጸዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለምን እየናጠ ባለበት ወቅት በርካታ ሀገራት በራቸውን ዝግ አድርገው መቀመጣቸው ይታወቃል፤ የጥንቃቄ እርምጃዎቹም የወጪ ንግድ እንዲስፋፋ የሚያበረታቱ አይደሉም፤ በከፍተኛ ሁኔታ ምርቶቻችንን የሚቀበሉ ሀገራት በኮቪድ በሽታ ክፉኛ ተጠቅተው እንደነበሩም አስታውሰዋል።

ስፔን፣ ኔዘርላንድ፣ እንግሊዝ እና ስካንዴኔቪያን አገራትን ጨምሮ የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ውስጥ ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ባለፉው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንቅስቃሴ እስከመገደብ ያደረሰ ክልከላን መተግበሩን አመልክተዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያን ምርት በብዛት የሚቀበሉ እንደተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሌሎች የአረብ ሀገራት ላይ ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ችግሮች ነበሩ ያሉት አቶ ወንዳለ፣ ይህ ሁሉ እያለ ኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ላይ ጥሩ እየሰራች ነው ብለዋል።