አፍሪካዊያን ፖሊሲ አውጭዎች “የመረጃ መረብ ደህንነት” ላይ በትብብር እንዲሰሩ ተጠየቀ

ዶ/ር አህመዲን መሃመድ

ግንቦት 16/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የመረጃ መረብ ደህንነት ስብሰባ ላይ አፍሪካዊያን ፖሊሲ አውጭዎች “የመረጃ መረብ ደህንነት” ላይ በትብብር እንዲሰሩ ጠየቀች።

10ኛው አለም አቀፍ የመረጃ መረብ ደህንነት ስብሰባ አፍሪካ 2021 በበይነ መረብ እየተካሄደ ሲሆን፣ በመረጃ መረብ ደህንነትና የዲጂታል ጠላፊዎች ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡

የአፍሪካን የመረጃ መረብ ደህንነት ሁኔታ ያብራሩት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አህመዲን መሃመድ አፍሪካ በበይነ መረብ ግንኙነት ተደራሽነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ብትሆንም በመረጃ መረብ መንታፊዎች በአመት እስከ 3.5 ቢሊየን ዶላር እንደምታጣ ተናግረዋል፡፡

ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት በ469 ሚሊየን ገደማ የሞባይል ተጠቃሚያዎች 456 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር የገንዘብ ዝውውር እንደሚፈፀም ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ይህ እያደገ የመጣው የሞባይል የገንዘብ ዝውውር የመረጃ መረብ መንታፊዎች ዓይን ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል ብለዋል፡፡

አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ድርጅቶች የመረጃ መረብ ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዳልሆነና የፖሊሲ አውጭዎች በትኩረትና በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የበይነ መረብ ግንኙነት እየጨመረ መምጣት፣ በመረጃ መረብ ደህንነት ላይ በቂ ግንዛቤ አለመኖር፣ ዝቅተኛ የዲጂታል እውቀት፣ የመረጃ መረብ ጥበቃ ባለሙያ እጥረት፣ ፍቃድ የሌላቸው ሶፍትዌሮችን መጠቀም የአፍሪካን የመረጃ መረብ ለመንታፊዎች እንዲጋለጥ አድርጎታል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካን የበይነ መረብ ደህንነት ለማስጠበቅ ከአፍሪካ 2063 አጀንዳ ጋር በተጣጣመ መልኩ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንም ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል፡፡

በሂደት ላይ ያለው የአፍሪካ የአይ ሲ ቲ ዕድገት ህግና ፖሊሲ፣ የኢንተርኔት መንግስት ሰነድ መዘጋጀቱ፣ የመረጃ መረብ ደህንነትና የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ (ማላቦ ኮንቬንሽን)፣ የመረጃ ደህንነት ዳሰሳ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የመረጃ መረብ ደህንነት ስብሰባ የመረጃ መረብ ደህንነት ላይ ትኩረት በማድረግ  በየአመቱ የሚካሄድ መሆኑን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።