ለግድቡ በፍጥነት መጠናቀቅ ዳያስፖራው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

 

ግንቦት 16/2013 (ዋልታ) – በጣሊያንና አካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በጣሊያን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሚቱ ሐምቢሳ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመሆን ለግድቡ ድጋፍ ማድረግ እና የተከፈተባቸውን ሐሰተኛ የሚዲያ ዘመቻ መመከት ከቻሉ የማይቋቋሙት ጫና አይኖርም ብለዋል፡፡

አምባሳደሯ ለግድቡ በፍጥነት መጠናቀቅ ዳያስፖራው በቦንድ ግዢ፣ በስጦታ እና በዓይነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው በበኩላቸው፣ ሀገሪቱ በፍትሃዊነት በጋራ የመጠቀም ፖሊሲ እንደምታራምድ እና የዓባይ ውሃ የአስራ አንዱም የተፋሰሱ ሀገራት ሃብት ነው ብላ እንደምታምን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ሁሉም ይህን የተፈጥሮ ሃብት ምክንያታዊ በሆነ መንገድ አልምቶ የመጠቀም መብት እንዳለው እና ኢትዮጵያም እየደረሰባት ያለውን ጫና ተቋቁማ የግድቧን ግንባታ ከ80 በመቶ በላይ ማድረሷን ገልጸዋል።

ነገር ግን የታችኞቹ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ይህን አቋም ባለመቀበል በኢትዮጵያ ላይ ጫና እየፈጠሩ እንደሆነ በመጥቀስ፣ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ይህን ጫና ለመመከት ከመቼውም የበለጠ የተጠናከረ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተዘጋጀው ውይይት ከ180 በላይ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል::