በሰሜን ካሮላይና የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ከ41 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረጉ

ግንቦት 17/2013 (ዋልታ) – በሰሜን ካሮላይና ግዛት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ከ41 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረጉ፡፡

ድጋፉን የሰሜን ካሮላይና የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ድጋፍ አሰባሳቢ ግብርኃይል ተወካዮች በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተገኝተው አስረክበዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ፍጹም አረጋ በርክክቡ ወቅት ለአስተባባሪዎቹ እና ድጋፍ ላደረጉ ወገኖች ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ያልተገባ ጫና ለማክሸፍ የተደራጀ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በማቋቋም እንዲሰሩም ጠይቀዋል።

የግብርኃይሉ አስተባባሪዎቹ በበኩላቸው፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።

በቅርቡም በግዛቱ የሚኖሩ የዳያስፖራ ወገኖች የሚሳተፉበት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ፣ የቢዝነስ እና የድጋፍ ማሰባሰቢያ መድረክ ለማዘጋጀት ስምምነት ላይ መደረሱን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።