ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን በገበያ ሲያዘዋውሩ የነበሩ አካላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ

ሚያዝያ 17/2014 (ዋልታ) በትንሳኤ በዓል ዋዜማ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን በገበያ ሲያዘዋውሩ የነበሩ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ከዋልታ ጋር በስልክ ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ በትንሳኤ በዓል ዋዜማ በገበያ ውስጥ 13 ሺሕ 400 ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ሲያዘዋውሩ የነበሩ አምስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

ግለሰቦቹ በከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች መያዛቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም በዋዜማው እና በትንሳኤ በዓል እለት በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን ተናግረዋል፡፡

በመጪዎቹ ቀናትም የሚከበሩትን የኢድ አልፈጥር እና የዳግመ ትንሳኤ በዓላትን በተመለከተ የፀጥታ ችግር እንዳያጋጥም የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፍተኛ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አመላክተዋል።

ኅብረተሰቡም በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ ከፀጥታ አካላት ጋር በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሜሮን መስፍን

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW