ሀገር በቀሉ ፍራንኩን ኢት አውቶሞቲቭ ኢንጅነሪንግ የከባድ መኪና ምርት ኤክስፖርት አደረገ

ግንቦት 16/2014 (ዋልታ) ሀገር በቀሉ ፍራንኩን ኢት አውቶሞቲቭ ኢንጅነሪንግ ለ15ተኛ ዙር የከባድ መኪና ምርት ኤክስፖርት አድርጓል፡፡

ድርጅቱ ለ15ኛ ዙር ከባድ መኪናዎችን ኤክስፖርት ማድረጉን በተመለከተ በወዳጅነት አደባባይ ባዘጋጀው ማሳያ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በዓለማችን የትኛውም ሀገር ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች አሁን ካሉበት የከፍታ ደረጅ የደረሱት በስራ ወቅት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንደ መውጫ መንሰላል በመጠቀም ነው ሲሉ ተናግለዋል፡፡

ኢንዱስትሪዎች ለሚገጥሟቸው ችግሮች እጅ መስጠት ሳይሆን ለችግሮቹ የመፍትሔ ሀሳብ አፍላቂዎች መሆንና ያጋጠሙን ችግሮች ለስራችን መሻሻልና ዕድገት ጠቃሚ ግብዓቶች ናቸው ብሎ በመውሰድ ጠንክሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ፍራንኮን የጀመረው ስራ ተስፋ ሰጭ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ ድርጅቱ የማምረት አቅሙን ከገበያ ፍላጎቱ ጋር አጣጥሞና መጠንኑን ጨምሮ እንዲሰራ እና መሰረታዊ የሚባሉ የመኪና ክፍሎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ማምረት እንዲሸጋገር አሳስበው መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡

የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ፍራንችስኮ ቪሎኒ ድርጅቱ ከተቋቋመ አስር ዓመታትን ያሳለፈ መሆኑን ገልጸው ዛሬ ወደ ውጪ የተላኩትን ከባድ መኪናዎች ጨምሮ ከ15 በላይ የሚሆኑ መኪናዎችን ወደ ጎረቤት ሀገራት ልኳል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡