ሁለቱ ተቋማት በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ

ሰኔ 1/2014 (ዋልታ) የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሲቭል አቪየሽን ባለስልጣን ጋራ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ።

የአቪየሽን ቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ እና የአቪየሽን ኢኖቬሽን ማበረታቻ ድጋፍና እውቅና ማዕቀፍ ላይ ነው በጋራ ለመስራት የተፈራረሙት።

ስምምነቱን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ሲቭል አቪየሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታችው መንግሥቴ ተፈራርመዋል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ስምምነቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ ኢኮኖሚ እና ማኅበረሰብ ለመገንባት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሲቭል አቪየሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታችው መንግሥቴ ስምምነቱ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች የፋይናንስ፣ የፋሲሊቲ እና የማበረታቻ ድጋፍ እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል።

ባለስልጣኑ ከተለያዩ አካላት ጋር እንዲሁም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ የሥራ እንቅስቃሴ ለማድረግ ዝግጅት ማድረጉ ተመላክቷል።

በእመቤት ንጉሤ