ሁለንትናዊ የብልፅግና ጉዟችን በፅንፈኞች ሴራ አይደናቀፍም – ኦሮሚያ ክልል

መጋቢት 22/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሁለንትናዊ የብልፅግና ጉዟችን በፅንፈኞች ሴራ አይደናቀፍም ሲል አሳሰበ፡፡

በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ቆርኬ/አውራ ጎዳና በሚባለው ልዩ ሥፍራ በምንጃር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች በጉዞ ላይ በነበሩት የሕዝብ ሚሊሻና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይ ባደረሱት ዘግናኝ ጥቃት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባወጣው መገለጫ ገለጸ።

ከክልሉ መንግሥት የተሰጠ መግላጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ሁለንትናዊ የብልፅግና ጉዟችን በፅንፈኞች ሴራ አይደናቀፍም !

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መጋቢት 20/2014 በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ቆርኬ/አውራ ጎዳና በሚባለው ልዩ ሥፍራ በምንጃር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ  ኃይሎች በጉዞ ላይ በነበሩት የህዝብ ሚሊሻና የፌዴራል ፖሊስ ላይ ባደረሱት ዘግናኝ ጥቃት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ፤ ለተጎጂዎች ቤተሰቦችና ዘመዶቻቸው በሙሉ መጽጽናናትን ይመኛል፡፡

ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን ለማጠናከርና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ በሚንገኝበት በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ ዉስጥ ይህን መሰል ዘግናኝ ድርጊት መፈጸሙ የጽንፈኞቸን እኩይ ዓላማና ተግባር ይበልጥ ያጋለጠ ነዉ፡፡ የነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች እኩይ ተግባርና ሴራ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ዘላቂ አብሮነትና ሁለንተናዊ ብልጽግና ጉዞን ለማደናቀፍ የተወጠነ  የጥፋት ዕቅድ አካል መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች የህብረ-ብሔራዊ አንድነትና የህዝቦች አብሮነት ጸር መሆናቸዉን በቅጡ ስለምንረዳ አምርረን የምንታገላቸውና ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ጋር በመተባበር በህግ ፊት አቅርበን ተገቢና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማድረግ በቁርጠኝነት እንሠራለን፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመሆን ጥቃቱ በደረሰበት ቦታ ላይ ተገቢውን  ክትትል በማድረግ ወንጀለኞችን ህግ ፊት ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን እየገለጽን፣ መላው ህዝብ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን፡፡